ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ
አዲስ አበባ
አቤቱታ አቅራቢ ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ (Human Rights First)
(በአዋጅ ቁጥር 1113/11 መሰረት በህግ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተመስርቶ በምዝገባ ቁጥር 4116 ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት ያገኘ ሃገር በቀል የሲቪል ማህበር)
አድራሻ ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 04 የቤት ቁጥር አዲስ
ተጠሪ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር
አድራሻ ትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ሓወልቲ ክ/ከተማ
በአዋጅ ቁጥር 798/2013 ዓንቀፅ 5 (3) መሰረት ከኢፌዲሪ ህገ መንግስት ዓንቀፅ 9 (1) እና 37ጋር የሚቃረን ደንብ እንዲሻር የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጠው ስለማመልከት
ከጥቅምት 24/2013 ዓ/ም ጀምሮ የትግራይ ሃይሎች በአንድ በኩል እንዲሁም የአትዮጵያ ሃይሎችና አጋሮቻቸው መካከል የዘለቀው ጦርነት ጥቅምት 23/2015 ዓ/ም በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት በፕሪቶርያ ደቡብ አፍረካ በተደረገ ስምምነት ከቆመ በኃላ ከስምምነቱ በፊት ማለትም በጦርነቱ ወቅት የፌዴራል ህገ መንግሰቱ በመቃረን የወጡ ህጎች የተሻሩ መሆናቸው ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም በጦርነቱ ወቅት ስልጣን ባልተሰጠው ምክር ቤት የወጡ ኢ ህገ መንግስታዊ የሆነ ህጎች ተፈፃሚነታቸው የቀጠለ በመሆኑ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
በጦርነቱ ወቅት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በፈረሰው ምክር ቤት የወጡ አዋጆችእንዲሁም በክልሉ በነበረው ካቢኔ የወጡ ደንቦች ያለ ምንም ልዩነት ሙሉ በሙሉ ሊሻሩ ይገባል፡፡
በግዚያዊ አስተዳደሩ ከህዳር 28/03/2016 ዓ/ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንዲሆን የወጣው ደንብ ቁጥር 4/2016 በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የህገ መንግሰቱን ዓንቀፅ 9 (1) እና ዓንቀፅ 37 የሚቃረን ነው፡፡ ምክንያቱም
1ኛ ደንቡ ዜጎች በህገ መንግሰቱን ዓንቀፅ 37 የተረጋገጠላቸውን ፍትህ የማግኘት የማግኘት መብት በእጅጉ የሚነፍግ ነው፡፡
የደንቡ የመሸጋገርያ ክፍል ዓንቀፅ 11 (3) በግልፅ ከጥቅምት 24/ 2013 ዓ/ም እስከ ህዳር 30/ 2015 ዓ/ም ያለ የመንግስት ሰራተኛ፣ የግል ተቋማት ሰራተኛና የግለሰብ ሰራተኛ ውዝፍ ደመወዝ የሚመለከት አዲስ ክስ ጉዳይ ታግዶ ይቆያል፡፡ በተመሳሳይ በሂደት ላይ ያሉ የክስ፣ ይግባኝና የአፈፃፀም ጉዳዮች በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተጠንቶ መፍትሄ እስከሚደረግበት ባለበት ቆመው ይገኛሉ፡፡
2ኛ የደንቡ የመሸጋገርያ ክፍል ዓንቀፅ 11 (2) በፈረሰው የክልሉ ምክር ቤት የወጣውን እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 360/2014 ከመደበኛ ህጎች ጋር ተመዛዝኖ እስከሚሻሻል ድረስ ተፈፃሚነት ይኖረዋል በሚል በግልፅ ተፈፃሚነቱ እንደሚቀጥል ተገልጧል፡፡
በመሆኑም የደንቡ ዓንቀፅ 11 (3) በግልፅ የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብት የሆነው ፍትህ የማግኘት መብት በግልፅ የሚገድብ ነው፡፡ የህግ መንግሰቱ ዓንቀፅ 37 (1) ማነኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፡፡ ስለሆነም ስልጣን ባልተሰጠው አካል ለዛውም በደንብ ዜጎች ያላቸው የፍትህ ጥያቄዎች መገደብ ዜጎች መብታቸውን በፍርድ ቤት ወይም ሌሎች የዳኝነት አካላት እየቀረቡ መብታቸው ለማስከበር ያላቸው መብት ይገድባል፡፡
3ኛ ግዚያዊ አስተዳደሩ በደንብ የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት ለመገደብ ስልጣን አልተሰጠውም፡፡ በየትኛው ስልጣኑ ይህ ደንብ እንዳወጣው የተገለፀ ምንም ዓይነት አዋጅ ባልተገለፀበት በአንድ ተራ ደንብ በዓለም ዓቀፍ ኮንቬንሽንና በህገ መንግስት የተረጋገጠው ግዙፍ መብት የሆነውን ፍትህ የማግኘት መብት መገደብ ኢ ህግ መንግስታዊ ስለሆነ አዋጁ ሊሻር ይገበዋል፡፡
ዜጎች በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ካላቸው ለፍርድ ቤት በማቅረብ እንደ የጉዳዩ እየታየ መወሰን ሲገባው ገና ለገና ጉዳዮች በፍርድ ቤት እንዳይታዩ ለመከልከል የተደረገው ክልከላ ተገቢነት የሌለውና ህገ መንግስቱን የሚጥስ ስለሆነ ሊሻር የሚገባው ነው፡፡
4ኛ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጦርነት ከመቀሰቀሱ በፊት በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ፖሊስ ኮሚሽን ስር ሲሰሩ የነበሩ የፖሊስ አባላት ያለምንም ሕጋዊ ምክንያት ወደ ስራቸው እንዳይመለሱ እንደተደረጉ እና ደመወዛቸውም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳልተሰጣቸውና ከነቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን የጥሰቱ ተጠቂ ከሆኑ የትግራይ ፖሊስ አባላት ድርጅታችን ለማረጋገጥ ችሏል። ቁጥራቸው ከ1000 በላይ የሚሆኑ እሰከ 30 ዓመት ያገለገሉ የትግራይ ክልል የፖሊስ አባላት ከስራቸው እንዲባረሩ ያደረገው ደግሞ ነባሩ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ፈርሶ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 360/2014 እንደ አዲስ እንደተቋቋመ እና የሚመለመሉ የፖሊስ አባላትም ከትግራይ ሰራዊት ብቻ መሆኑ አዋጁ ስለሚያስገድድ ነባር የፖሊስ አባላት አዋጁ የማያካትታቸው ስለሆነ ነው፡፡
5ኛ የፕሪቶርያ ስምምነት ሁሉም ነገር ወደ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲመለስና በሕገ መንግስቱ እና ሕገ መንግስቱን መሠረት በወጡ አዋጆችና በሌሎች ሕጎች ሁሉም እንዲመራ የሚያስገድድ ቢሆንም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ይህን ስምምነት በመጣስ በኢትዮጵያ እና በክልሉ ሕጎች መሠረት የተቀጠሩና የሰለጠኑ፣ ለዓመታት ያገለገሉ የፖሊስ አባላት በትጥቅ ትግል አልተሳተፉም በማለት ከስራ ማባረሩ ወይም ወደ ስራ እንዳይመለሱ መከልከሉ፣ እንደ ማንኛውም የፖሊስ አባላት የጥሮታ እና የሌሎች ማህበራዊ ዋስትና ጥበቃ እንዳያገኙ መከልከሉ ከስምምነቱ ውጭ የሆነ ተግባር የአገሪቱ ሕገ መንግስትን፣ የክልሉ ሕገ መንግስትንና ሌሎች ሕጎችን እና አገሪቱ የተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን እየጣሰ መሆኑ ያመላክታል፡፡
6ኛ የፖሊስ አባላቱ ለማባረር ምክንያት የሆነው የክልሉ አዋጅ ቁጥር 360/2014 በጦርነቱ ወቅት በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ሕገ መንግስታዊ አይደለም ተብሎ በፈረሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ነው፡፡ ሕገ መንግስታዊ አይደለም በተባለ ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ደግሞ ሕጋዊ ሆኖ ተፈፃሚነቱ የሚቀጥልበት አግባብ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ አዋጅ ቀድሞ በስራ ላይ በነበሩ የፀኑ ሕጎች መሠረት የተመለመሉ እና ሲያገለግሉ በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ በርካታ የመብት ጥሰት መቀጠሉ ሕጋዊነት የሌለው ተግባር መሆኑ ድርጅቻችን ተገንዝቧል።
ስለሆነም የደንቡ የመሸጋገርያ ክፍል ዓንቀፅ 11 (2) በፈረሰው የክልሉ ምክር ቤት የወጣውን እና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ቁጥር 360/2014 ከመደበኛ ህጎች ጋር ተመዛዝኖ እስከሚሻሻል ድረስ ተፈፃሚነት ይኖረዋል በሚል በግልፅ ተፈፃሚነቱ እንደሚቀጥል ያመለካተ ስለሆነ የህገ መንግሰቱ ዓንቀፅ 9 (1) ማለትም ህግ መንግሰቱ የሃገሪቱ የበላይ ህግ ነው፡፡ ማነኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም በሚል የተገለፀውን የህገ መንግስቱ የበላይነት የሚሸረሽር ስለሆነ ደንቡ ደግሞ በግልፅ የሚፃረር ስለሆነ እንዲሻር እንጠይቃለን፡፡
ከህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የምንጠይቀው ዳኝነት
ከላይ በዝርዝር እንዳቀረብነው በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የወጣውን ከህዳር 28/03/2016 ዓ/ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንዲሆን የወጣው ደንብ ቁጥር 4/2016 የህገ መንግሰቱን ዓንቀፅ 9 (1) እና ዓንቀፅ 37 የሚቃረን ስለሆነ የህገ መንግስት ትርጉም ስለሚያስፈልገው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ እንዲደረግ እናመለክታለን፡፡
የማስረጃ ዝርዝር
ሀ) የሰው
1) ረዳት ፕሮፌሰር ሙሴ መዝገቦ ገብረመድህን አድራሻ አዲስ አበባ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 9 (የደንቡ ኢ ህግ መንግስታዊነት በተመለከተ ማብራርያ የሚሰጡ የህግ ባለሙያ)
ለ) የሰነድ
1) ደንብ ቁጥር 4/2016 13 ገፅ
2) ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ (Human Rights First) በአዋጅ ቁጥር 1113/11 መሰረት በህግ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተመስርቶ በምዝገባ ቁጥር 4116 ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት ያገኘ ሃገር በቀል የሲቪል ማህበር ስለመሆኑ የሚያሳይ ፈቃድ 01 ገፅ
