መግብያ
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በቁጥር 4118 በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ደርጅት የተመዘገበና እውቅና ያገኘ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እየሠራ ይገኛል። አሁንም በወቅታዊ የጸጥታ ተቋማት አባላት የመብት አያያዝ ላይ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተገኘ መረጃ መሠረት መረጃውን በመመርመርና በመተንተን የአባላቱ ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ እንደሚከተለው አጭር ሪፖርት በማጠናቀር አቅርቧል።
የፕሪቶርያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆምና የሰላም ስምምነት በፌዴራል መንግስቱ እና በህወሓት ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ አንድ ዓመት አልፎታል፡፡ ስምምነቱ በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም በማድረግ ተጨማሪ ሞት፣ አካል ጉዳተኝነት፣ መፈናቀል፣ ስቃይ እና የንብረት ውድመት እንዳይከሰት አድርጓል። ነገር ግን አሁኑም ስምምነቱን መሠረት በማድረግ፣ በአገሪቱ ሕገ መንግስት፣ አዋጆች እና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ያልተፈፀሙ በርካታ ጉዳዮች ያሉ ሲሆኑ ስምምነቱን ተግባራዊ ባለመደረጉ በርካታ ዜጎች እንደሚከተለው ለተለያዩየመብት ትሰቶች ተጋልጠዋል።
በትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በፖሊስ አባላት ላይ እየቀጠለ ያለው የመብት ጥሰት
በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጦርነት ከመቀሰቀሱ በፊት በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ፖሊስ ኮሚሽን ስር ሲሰሩ የነበሩ የፖሊስአባላት ያለምንም ሕጋዊ ምክንያት ወደ ስራቸው እንዳይመለሱ እንደተደረጉ እና ደመወዛቸውም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳልተሰጣቸው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መሆናቸውን የጥሰቱ ተጠቂ ከሆኑ የትግራይ ፖሊስ አባላት ድርጅታችን ለማረጋገጥ ችሏል።
ቁጥራቸው ከ1000 በላይ የሚሆኑ የቀድሞ የትግራይ ክልል የፖሊስ አባላት በተለያየ ጊዜ በቅርባቸው ወደ ሚገኝ የወረዳ ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱና ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው አቤቱታ ያቀረቡ መሆናቸውን በድርጅታችን ለማወቅ የቻለ ሲሆን ባደረግነው የማጣራት ሥራ ቁጥራቸው 505 የሚሆኑ የትግራይ ክልል ፖሊስ አባላት ስም ዝርዝራቸው እና ያቀረቡት አቤቱታ፣ እንዲሁም የተሰጣቸው ምላሽ በእጃችኝ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከመላው የትግራይ ክልል አከባቢዎች የተወጣጡ በቁጥር 244 የሆኑ የፖሊስ አባላት ለትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ለኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ2 ተቋም መቐለ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት፤ በምስራቅ ዞን የሚገኙ በቁጥር 46 የፖሊስ አባላት፤ በምዕራብ ዞን ሑመራ፣ ወልቃይት፣ ማይጋባ፣ ቆራሪት እና በተለያዩ አከባቢዎች ሲያገለግሉ የነበሩ በቁጥር 24 የሆኑ የፖሊስ አባላት፤ በወረዳ ጣንቋ አበርገለ በቁጥር 28 የሆኑ የፖሊስ አባላት፤ በማእከላዊ ዞን አክሱም ከተማ አከባቢ በቁጥር 15 የፖሊስ አባላት፣ በዓድዋ ከተማ እና አከባቢው በቁጥር 51 የሆኑ የፖሊስ አባላት፣ በየጭላ አከባቢ በቁጥር 21 የሆኑ የፖሊስ አባላት፤ በቆላ ተምቤን አከባቢ በቁጥር 24 የሆኑ የፖሊስ አባላት፤ እና በሰሜን ምዕራብ ዞን ሽረ እንዳስላሰ ከተማ በቁጥር 28 የሆኑ የፖሊስ አባላት በአጠቃላይ 505 የፖሊስ አባላት ወደ ሥራ ገበታ እንዲመለሱና ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው አቤቱታ በየዞናቸው ለሚገኙ የአስተዳር እርከኖች ማቅረባቸው ድርጅታችን ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም አቤቱታ ያላቀረቡና በየቤታቸው ያለ ሥራ የተቀመጡ ከነቤተሰቦቻቸው ስቃይ ውስጥ ያሉ በርካታ የትግራይ ፖሊስ አባላት መኖራችውን የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ካነጋገራቸው የፖሊስ አባላት ለመረዳት ችሏል።
የፖሊስ አባላት ላቀረቡት አቤቱታም የሚከተሉት ምላሾች በተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች እንደተሰጣቸው ድርጅታችን ባደረገው ማጣራት ለማረጋገጥ ችሏል።
1. በትግራይ ክልል የማእከላዊ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም በደ.ቁ. 772/715/81/01 ለሁሉም የዞኑ ወረዳዎች በአስተላለፈው ደብዳቤ መሠረት ከመጀመርያው ወደ ትግል ያልገቡ (የከዱ) የክልሉ የፖሊስ አባላት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ምንም ዓይነት ደመወዝ ሳይከፈላቸው በነበሩበት ይቆዩ በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
2. የፅምብላ ወረዳ አስተዳደር ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም በአድራሻ ለለእነ ም/ኢ/ር ፅጋብ አስፈሀ በፃፈው ደብዳቤ መሠረት የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የደመወዝ አፈፃፀም መመርያ ቁጥር 1/2015 አንቀፅ 8.1 እና 3 የፖሊስ ደመወዝ ክፍያ የሚመለከታቸው ከሰራዊት የሚቀነሱ እና በትግሉ የተሳተፉ ብቻ ስለሚል በማለት ሌሎች የፖሊስ አባላት ደመወዛቸውእንዳይከፈላቸው በማለት ምላሽ ሰጥቷል።
3. የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥር 244 የሆኑ የፖሊስ አባላት ለቀረበለት ወደ ሥራ ገበታ እንመለስ እና ደመወዛችን ይከፈለን የሚል አቤቱታ መልስ አልሰጠም።
4. በትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መልስ ያልተሰጣቸው 244ቱ የፖሊስ አባላት ሰኔ 21 ቀን 2015 ዓ.ም እና ሐምሌ 21 ቀን 2015 ዓ.ም አቤቱታ ለኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም መቐለ ቅርንጫፍ አቅርበው ተቋሙ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በደ/ቁ. እንባ/ቅ/879/አ.9879/15 የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለአቤቱታ አቅራቢዎች ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጥ በደብዳቤ አሳውቋል። ይህን ተከትሎ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋሙ ሐምሊ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ ነባሩ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ፈርሶ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 360/2014 እንደ አዲስ እንደተቋቋመ እና የሚመለመሉ የፖሊስ አባላትም ም ከትግራይ ሰራዊት ብቻ መሆኑ አዋጁ ስለሚያስገድድ ነባር የፖሊስ አባላት አዋጁ የማያካትታቸው መሆኑን በመጥቀስ ደመወዝ ሆነ ቅጥር3 እንደሌላቸው ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የፖሊስ ኮሚሽኑ የጻፈው ምላሽም ለአቤቱታ አቅራቢ የፖሊስ አባላት ቆይቶ እንደደረሳቸው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅታችን ለመረዳት ችሏል።
5. ከዚህ መልስ በኃላ ግን እነዚህ ነባር የፖሊስ አባላት መፍትሔ አጥተው ደመወዝ ተከልክለው በአቤቱታ እየተንከራተቱና ቤተሰቦቻቸው ለማህበራዊ ችግሮች እንደተጋለጡ ድርጅታችን ለማወቅ ችሏል።
የተፈፀሙ የሕግ እና የመብት ጥሰቶች
- የፕሪቶርያ ስምምነት ሁሉም ነገር ወደ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት እንዲመለስና በሕገ መንግስቱ እና ሕገ መንግስቱን መሠረት በወጡ አዋጆችና በሌሎች ሕጎች ሁሉም እንዲመራ የሚያስገድድ ቢሆንም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን ይህን ስምምነት በመጣስ በኢትዮጵያ እና በክልሉ ሕጎች መሠረት የተቀጠሩና የሰለጠኑ፣ ለዓመታት ያገለገሉ የፖሊስ አባላት በትጥቅ ትግል አልተሳተፉም በማለት ከስራ ማባረሩ ወይም ወደ ስራ እንዳይመለሱ መከልከሉ፣ እንደ ማንኛውም የፖሊስ አባላት የጥሮታ እና የሌሎች ማህበራዊ ዋስትና ጥበቃ እንዳያገኙ መከልከሉ ከስምምነቱ ውጭ የሆነ ተግባር የአገሪቱ ሕገ መንግስትን፣ የክልሉ ሕገ መንግስትንና ሌሎች ሕጎችን እና አገሪቱ የተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን እየጣሰ መሆኑ ያመላክታል፡፡
- የፖሊስ አባላቱ ለማባረር ምክንያት የሆነው የክልሉ አዋጅ ቁጥር 360/2014 በጦርነቱ ወቅት በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ሕገ መንግስታዊ አይደለም ተብሎ በፈረሰው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ነው፡፡ ሕገ መንግስታዊ አይደለም በተባለ ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ደግሞ ሕጋዊ ሆኖ ተፈፃሚነቱ የሚቀጥልበት አግባብ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ሕገ መንግስታዊ ባልሆነ አዋጅ ቀድሞ በሥራ ላይ በነበሩ የጸኑ ሕጎች መሠረት የተመለመሉ እና ሲያገለግሉ በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ በርካታ የመብት ጥሰት መቀጠሉ ሕጋዊነት የሌለው ተግባር መሆኑ ድርጅቻችን ተገንዝቧል።
በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ተቋማት በሚሰሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ እየቀጠለ የሚገኝ የመብት ጥሰት
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከትግራይ ክልል ውጭ በተለይም በአዲስ አበባ በተለያዩ የፀጥታ ተቋማት ማለትም በመከላከያ ሚኒስቴር፣ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ በፌዴራል ማረምያ ቤቶች፣ በብሔራዊና መረጃ ደህንነት አገልግሎት፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ እና በየግል የደህንነት አገልግሎት ሥራ ላይ ሲሰሩ የነበሩት የትግራይ ተወላጆች በማንነታቸው ተለይተው እንዲታሰሩ እና ከሥራ እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡ የመታሰራቸው ምክንያትም በመንግስት ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም። ይህ እንዳለ ሆኖ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ወዲህ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ከፍተኛ የመብት ጥሰቶች ላይ የመቀነስ ሁኔታ ያሳየ ቢሆንም አሁንም በፌዴራል መንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ውስጥ በሚሠሩ የትግራይ ተወላጅ አባላት ላይ የመብት ጥሰቱ እንደሚከተለው ቀጥሏል።
በትግራይ ተወላጅነታቸው ምክንያት ደመወዝ እየከፈሉ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዳይመለሱና እንዳይሰሩ የተከለከሉ የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ከ400 በላይ እና በፌዴራል ፖሊስ ከ500 በላይ የፖሊስ አባላት እንዳሉ ድርጅታችን ለማወቅ ችሏል። በዚህም የአባላቱ የመስራትና የማገልግለ መብታቸው ከመጣሱ በተጨማሪ ለከፍተኛ ስነ ልቦናዊ ችግሮች እንደተጋለጡ ድርጅታችን ከአባላቱ ለመረዳት ችሏል። እንዲሁም ከነበረባቸው የሙያዊ ኃላፊነቶች እንዲወርዱ፣ የደረጃና የማዓረግ እድገቶች እንዳያገኙ፣ ማግኘት ያለባቸው ጥቅማ ጥቅም እንዳያገኙ እና በአባልነታቸው ምክንያት ካገኙት የመኖሪያ ቤት በግድ እንዲወጡና ቤተሰቦቻቸው ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጡ፣ እንዲሁም መኖሪያ ቤቶቹ ከሕግ ውጪ ለሌሎች አባላት እንዲተላለፉ ተደርጓል።
በአጠቃላይ በፌዴራልና አዲስ አበባ በሚገኙ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት የሚሰሩ ወደ ስራ ያልተመለሱ የትግራይ ተወላጆች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ፣ እስካሁን ያልተሰጣቸው ጥቅማና ጥቅም እንዲሁም በአባልነታቸው ተሰጥዋቸው የነበረው መኖሪያ ቤቶች እንዲሰጣቸው ወይም በምትክ ተለዋጭ እንዲሰጣቸው ድርጅታችን በአበክሮ ይጠይቃል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽን የትግራይ ተወላጆች አባላት በተመለከተ
ጦርነቱ ከተጀመረበት ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ማግስት ጀምሮ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሆኑት የትግራይ ተወላጆች ትጥቃቸው፣ የደንብ ልብሳቸው፣ መታወቂያቸው፣ ዱላቸው እንዲሁም ማንኛውም የፖሊስ አባላት መሆናቸውን የሚያሳይ ሁሉም ንብረቶች እንዲወሰዱ ከተደረገ በኃላ ጡረታ የወጡትን ጭምር ለእስር እንዲዳረጉ እንደተደረገ ድርጅቱ አረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ 730 የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሆኑት የትግራይ ተወላጆች በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ3 ወር ከ10 ቀናት እንዲታሰሩ የተደረገ ሲሆን በሁለት ዓመታት የጦርነቱ ጊዜ እነዚህ የፖሊስ አባለት በተለያዩ ወታደራዊ ካምፖችና የፖሊስ ማሰልጠኛዎች ከ5 ወራት በላይ ያለ አንዳች የወንጀል ክስ እና ፍርድ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በዚህ የእስር ጊዜያት በብሄራቸው ምክንያት ድብደባ፣ ስድብ፣ ዛቻና ማስፈራራት ይደርስባቸው እንደነበረ ከታሰሩት መካከል ለድርጅታችን ገልጸዋል፡፡
እነደዚሁም በኮልፌ ማሰልጠኛ በነበረው ቆይታም ጁንታውን ማውገዝ አለባችሁ ጁንታውን ያላወገዘ እና ያልተሳደበ እራሱ ጁንታ ነው የሚል ዘመቻ የነበረ ሲሆን በዚህም ምክንያት የፖሊስ አባላቱ ለእስርና ለከፍተኛ እንግልት የተዳረጉ ስለመሆናቸው ሳጅን ኢሳያስ የተባለ (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) የነበረው ሁኔታ አብራርቶ ገልፆልናል፡፡
እነዚህ በጦላይ ማሰሰልጠኛ ከ730 በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላት አሁን ግን በተለያየ ጫናና ምክንያት ቁጥራቸው እንዲቀንስ እየተደረገ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ማለትም ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት አንድ ዓመት በኃላም ቢሆን ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ አልተደረገም፡፡
ይህ ማለት ለሶስት ዓመት የነበረውን ደመወዛቸው ማለትም የሌሎች ብሄር ተወላጆች የሚያገኙት ጥቅማ ጥቅም ተቀንሶ እንዲሁም ምንም ዓይነት ማዓረግ እድገት ተከልክለው፣ የእርከን ጭማሪ ተከልክለው ለማህበራዊ ቀውስ ተዳርገው ይገኛሉ፡፡ ስራ መስራት እየቻሉ ስራ እንዳይሰሩ ተደርገው በቀን ሁለቴ ፈርመው ደመወዝ እንዲወስዱ ማድረግ በስነ ልቦናቸው ላይ ጫና እያሳደረባቸው እንደሆነ ያነጋገርናቸው የፖሊስ አባላት ገልፀውልናል፡፡
ስለሆነም እነዚህ በማንነታቸው ብቻ ስራ እንዳይሰሩ የተደረጉ የፖሊስ አባላት በመሰላቸት ስራቸው እንዲለቁ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ህገ ወጥ ስለሆነ እስከ አሁን ድረስ ያላገኙትን የመዓረግ እድገት ተጠብቆላቸው እርከናቸው ተጨምሮ ወደ ነበሩበት የስራ ኃላፊነት ሊመለሱ ይገባል፡፡
እንደዚህ ዓይነት በብሄር ማንነት የለየ አድልዎና መገለል በየትኛውም ግዜና ሁኔታ በማንም ሰው ላይ እንዳይደገም ጥንቃቄ እንዲደረግ እና ይህንን ውሳኔ የወሰኑ አካላት ላይ ተጣርቶ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ድርጅታችን ይጠይቃል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የትግራይ ተወላጆች አባላት በተመለከተ
በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም በተመሳሳይ መንገድ በየትግራይ ተወላጆች የፖሊስ አባላት ትጥቃቸውን፣ የደንብ ልብሳቸውን፣ መታወቅያቸውን፣ ዱላቸውን እንዲሁም ማንኛውም የፌዴራል ፖሊስ አባላት መሆናቸውን የሚያሳይ ሁሉም ንብረቶችን እንዲያስረክቡ ከተደረገ በኃላ ሁሉም አባላት ጡረታ የወጡትን ጭምር ታስረዋል፡፡
በአጠቃላይ ወደ ትግራይ ክልል በ2013 ዓ.ም ለሰላም ማስከበር በሚል የሄዱት በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ የፖሊስ አባላት ሳይጨምር 540 የፌዴራል ፖሊስ አባላት የሆኑት የትግራይ ተወላጆች በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ከ3 ወር በላይ እንዲታሰሩ የተደረገ ሲሆን በሁለት ዓመታት የጦርነቱ ጊዜ እነዚህ የፖሊስ አባለት በተለያዩ ወታደራዊ ካምፖችና የፖሊስ ማሰልጠኛዎች ከ5 ወራት በላይ ያለ አንዳች የወንጀል ክስ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በዚህ የእስር ጊዜያት ድብደባ፣ የአካል ጉዳት፣ ስድብ፣ ዛቻና ማስፈራራት ይደርስባቸው እንደነበረ ከታሳሪዎቹ መካከል ለድርጅቱ አብራርተዋል፡፡
የተፈፀሙ የሕግ እና መብቶች ጥሰቶች
- በአዲስ አበባ እና ፌዴራል ፖሊስ ተቋማት ወደ ስራ እንዳይገቡ መደረጉ የትግራይ ክልል በፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ስራ የመሳተፍ መብት የሚገድብ በመሆኑ የህገ መንግስቱ የዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ በእኩልነት የመሳተፍ መርህ የሚጥስ ነው፡፡
2. የፖሊስ አባላቱ ስራ አለመስራት ለሞራላዊ ውድቀት እና የመገለል ስሜት ይፈጥራል፡፡
3. ሕገ መንግስቱ እና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ያረጋገጠው የሥራ መብት ተጥሷል።
በፌዴራል መንግስት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በትግራይ ክልል መንግስት ሊወሰዱ የሚገቡ መፍትሔዎች
- የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራል መንግስት የፀጥታ ተቋማት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽን፣ የፕሪቶርያ ስምምነት በማክበር ሕገ መንግስታዊ ግዴታቸው እንዲወጡና በነበረው ጦርነት ምክንያት ከስራ የተፈናቀሉ ዜጎች በስምምነቱ እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት እንዲሁም በተቋቋሙባቸው አዋጆች መሰረት ከሥራ የተገለሉ የትግራይ ተወላጆች አባላት ወደ ነበሩበት የስራ ገበታ እንዲመልሱ፣ የተቋረጠባቸው ጥቅማ ጥቅም እንዲያከበሩ ድርጅታችን ይማጸናል።
- የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሕገ ወጥ ተብሎ በፈረሰ ምክር ቤት የወጣ አዋጅ ቁጥር 360/2014 የሚፀና ሕግ እንዳልሆነ በመቁጥር ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በነበረው ሕጋዊ አዋጅ መሰረት ከስራ የተገለሉ የፖሊስ አባላት ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመልስ፣ ያልተከፈላቸው ደመወዝ፣ ያልተሰጣቸው ጥቅማ ጥቅም ጨምሮ እንዲከፍል ድርጅታችን ይማጸናል፡፡ በአጠቃላይ በትግል አልተሳተፉም የሚል በሰላም ስምምነቱ የቀረ ጉዳይ አሁን እንደ ምክንያት በማምጣት የዜጎች መብት መጣስ እንዲያቁም እንማፀናለን፡፡
- ከዚህ በኃላም የፌዴራል መንግቱ ይሁን የአዲስ አበባ እና የትግራይ ክልል መንግስታት በማንኛውም ዜጋ ላይ ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይፈፀም ጥንቃቄ እንዲደረግ ድርጅታችን ይማጸናል።
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ
Human Rights First Ethiopia
ዋና ዳይሬክተር
