በአዲስ አበባ ከተማ ወጣት የትግራይ ተወላጀች ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ እስር በተመለከተ ከቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች የወጣ አጭር ሪፖርት

June 30, 2025 

ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

መግብያ

ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በቁጥር 4118 በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ደርጅት የተመዘገበና እውቅና ያገኘ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እየሠራ ይገኛል። ድርጅታችን ከዚህ በፊት የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም በትግራይ እና ኤርትራ ተወላጆች ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተካሄደ የዘፈቀደ እስር ሪፖርት በማውጣት ድርጊቱ እንዲቆም፣ የታሰሩ እንዲፈቱ እንዲሁም የዘፈቀደ እስራት እንዳይደገም ማረጋገጫ እንዲሰጥ ማሳሰቡ ይታወቃል። ነገር ግን እስራቱ ሚያዝያና ግንቦት ወራት ውስጥ ረገብ ካለ በኋላ እንደ አዲስ አገርሽቶ በተያዘው ሰኔ ወር ውስጥ በትግራይ ተወላጆች ላይ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህ ምክንያት ድርጅታችን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተገኘ መረጃ መሠረት ሰኔ/2017 ዓ/ም ላይ ባገረሸው የትግራይ ተወላጅነት መሠረት ያደረገ የዘፈቀደ እስር ላይ እንደሚከተለው አጭር ሪፖርት በማጠናቀር አቅርቧል።

የሪፖርቱ መነሻ

ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተማ በትግራይ ተወላጆች በተለይ ደግሞ ወጣቶች ላይ ከተለያዩ ቦታዎች እስር እየተፈፀመ እንደሆነ በማሕበራዊ ሚድያ ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ከሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ግን የቤተሰብ አባላት የታሰሩባቸው ሰዎች እንዲሁም እስራት የደረሰባቸው ወጣቶች ተደጋጋሚ ጥቆማ ለድርጅታችን በመስጠታቸው ምክንያት ትኩረት ሰጥተን ጉዳዩን ከተበዳዮች፣ ከምስክሮች እና ከጉዳዪ ጋር ቅርበት ካላቸው አካላት የተገኙ መረጃዎች በማሰባሰስብና በመተንተን እንደሚከለው ዝርዝር የማጣራት ግኝቱ አቅርበናል፡፡

እየተፈፀመ ያለ እስራት

የትግራይ ክልል ወጣቶችና ቢሮ በቅርብ ጊዜ ባወጣው ሪፖርት በዚህ ዓመት 2017 ዓ.ም ውስጥ ብቻ ከ56,000 (ሃምሳ ስድስት ሺ) ወጣቶች ከትግራይ ክልል በስደት እንደወጡ አረጋግጧል፡፡ ለስደቱ እንደ ዋና መነሻ ስራ አጥነት ሲሆን በተለይ ደግሞ በቅርብ ጊዜያት እየታየ ያለ ቅድመ የግጭት ምልክቶች ወጣቶች ከክልሉ ሸሽተው እንዲወጡ ተጨማሪ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ በዚህ የስራ አጠነትና የፖለቲካ አለመረጋጋት ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ የወጣቶቹ መዳረሻ ከሆኑት ቦታዎች መካከል አንዷ ነች፡፡

ሆኖም ግን ለሥራ ፍለጋና መረጋጋት መሻትን የመጡ ወጣቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ቦታዎች የዘፈቀደ እስር ሰለባ እየሆኑ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ እስሩ አዲስ ለመጡት ወጣቶች ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ከተማ ቋሚ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ወጣቶችም የዚሁ ሰላባ ናቸው፡፡ እስሩ የሚፈፀመው በስማቸው፣ በአነጋገር ሁኔታቸው፣ በቋንቋቸው እየተለዩ መሆኑን ታስረው ከተፈቱ ምስክሮች አረጋግጠናል፡፡

በምርመራ ወቅት ከተቀበልናቸው ምስክርነቶች በከፊል ፣ ፊልሞን ገብረመድህን (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) አዲስ አበባ መኖር ከጀመረ ወደ 10 ዓመት የሆነው ሲሆን ቋሚ የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው፡፡ያጋጠመውን ነገር እንደሚከተለው ይዘረዝራል

“ ነገር ግን ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በየካ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ኮተቤ 02 በሚባለው አከባቢ ከስራ ቦታ ወጥቼ ምሳ ልበላ በምሄድበት ወቅት መንገድ ላይ ሶስት የፖሊስ አባላት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን እያስቆሙ እየጠየቁ ነበር፡፡ መታወቂያ አለህ ወይ? በማለት ሲጠይቁኝ የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ሰጥሁዋቸው፡፡ ሆኖም የአባቴ ስም ገብረመድህን መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ከሌሎች ሰዎች መካከል ለይተው አንድ ቦታ እንድቀመጥ አዘዙኝ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ሌላ አንድ የትግራይ ተወላጅ አምጥተው ከእኔ ጋር ቀላቀሉት፡፡ ተነሱ ብለውን በአከባቢው ወደሚገኝ ወሰን አካባቢ ፖሊስ ጣብያ ጉዞ ጀምረን፡፡ መንገድ ላይ ሌላ 2 የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ተቀላቀሉን ጠቅላላ 4 ሁነን ጉዞ ቀጠልን፡፡ ከመካከላችን አንዱ ነገ የመንጃ ፈቃድ ፈተና እንዳለው በመግለፅ እንዲለቁት እያለቀሰ ሲለምናቸው ነበር፡፡ ችግር የለውም መዝግበን እንለቃችዋለን በማለት ፖሊስ ጣብያ ወሰዱን፡፡ ፖሊስ ጣብያው ጋር እንደደረሰን በግምት በቁጥር ከ40-45 የሚሆኑ ሌሎች የትግራይ ተወላጆች ታስረው ነበር፡፡ ከፖሊስ ጣብያው በየተራ ሾላ ገበያ አከባቢ ወደ ሚገኘው የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ህንፃ ወሰዱን፡፡ በግምት 12 በ10 ካ.ሜ ወደ ምትሆን ክፍል አስገቡን፡፡ በክፍሉ ውስጥ ከ50 እስከ 55 የሚሆኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከቀናት በኋላ ብዛታችን ወደ 87 ሰዎች ደረስን፡፡ ሁሉም የትግራይ ተወላጅ ናቸው፡፡ አብዛኛው ታሳሪዎቹ ከኮተቤ፣ ፈረንሳይ እና ወሰን ከተባሉ ሰፈሮች ታፍሶው የመጡ ናቸው፡፡ አንዳንዱ ሹፌር ሆኖ መኪናው ባቆመበት ታፍሶ የመጣ፣ መወልወያ፣ ፍራሽ፣ ሽቶ ሻጮች፣ የልብስ ስፌት እንዲሁም መምህራን ጭምር ነበሩ፡፡ የታሰርንበት ምክንያት የሚነግረን ሰው አልነበረም፡፡ የመታሰራችን ምክንያት የፖሊስ አባላቱን ስንጠይቃቸው ከላይ የመጣ ትእዛዝ ነው፣ እኛ ምንም አናውቅም ይሉን ነበር፡፡ ታሳሪ የቤተሰብ አባልን ለመጠየቅ የመጣ ጠያቂ ወጣት ከሆነ ወድያውኑ በመያዝ ወደ እኛ ያስገቡታል፡፡ ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው መጥቶ ሁላችን ስራችን፣ የተወለድንበት ቦታ ጠየቀን ከዛ በኋላ ከመካከላችን ውስጥ 7 ታሳሪዎችን እንዲፈቱ ተደረገ፡፡ አብዛኛው ሰው መታሰሩ ቤተሰቡን አያውቅም፡፡ ድንገት ከመንገድ ተይዞ የገባ ነው፡፡ ሰኞ የመጣው ሰውየ ደግሞ ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ተመልሶ መጣ፡፡ አሁንም ከጠያየቀን በኋላ እኔ ለብዙ ዓመታት አዲስ አበባ እንደኖርኩ፣ የስራ ማስረጃም ማምጣት እችላለሁ ካልኩት በኋላ ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያት ካቀረቡ ሰዎች ጋር ለይቶ እንድንቀመጥ አደረገን፡፡ በአጠቃላይ 17 የምንሆን ሰዎች ለይቶ እንዲፈቱን ትእዛዝ አስተላልፎ ሄደ፡፡ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ታስሬ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ተፈትቻለሁ፡፡ ከፖሊስ ጣብያው ስወጣ ከ100 በላይ ታሳሪ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ፡፡”

አቶ ገብረኪዳን ወልዳይ (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) በአዲስ አበባ ከተማ ን/ስ/ላፍቶ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ሃና ማርያም አካባቢ ነዋሪ የሆነ ጁብቲ እየተመላለሰ ራሱንና ቤተሰቡን የሚያስተዳድር የተሳቢ መኪና ሾፌር ነው፡፡ ነገር ግን ስራውን አከናውኖ ወደ ቤቱ በመሄድ ላይ እያለ በመንገዱ ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውሏል። የእስሩ ምክንያት ኤርትራዊ ነህ የሚል ሲሆን ለእስር ከተዳረገ በኋላ ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊ ነኝ ቢልም ሰሚ በማጣቱ ምክንያት ተቀጥሮ ከሚሰራበት ድርጅት የድርጅቱ ሰራተኛ ስለመሆኑ የሚገልጽ ደብዳቤ ተፅፎለት ከአምስት ቀናት በኋላ ከእስር ሊለቀቅ ችሏል፡፡

አቶ ሓየሎም (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) አዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ላም በረት አካባቢ በሚገኝ አንድ አነስተኛ ሆቴል ውስጥ በስራ አስኪያጅነት ተቀጥሮ የሚሰራ ግለሰብ ነው፡፡ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም አስቤዛ ለመግዛት ወደ ሾላ ገበያ በሄደበት ታፍሶ ከታሰረ በኋላ እስከ አሁን ፍ/ቤት ሳይቀርብ ማለትም ከአንድ ሳምንት በላይ ያለ ምንም ጥያቄና በቂ ጥርጣሬ በየካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምርያ በእስር ላይ ይገኛል፡፡ ለእስሩ የቀረበለት ምንም ዓይነት ወንጀል ጥርጣሬ የለም፡፡ ከዚህ እስር ጋር ተያይዞ አቶ ሓየሎምን ለመጠየቅ ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ወደ የካ ክ/ከተማ ፖሊስ መምርያ ፖሊስ ጋር የሄደ የቅርብ ዘመድ ለቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ድርጅት እንደገለፀው ወደ 100 የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች በተመሳሳይ ምክንያት በፖሊስ ጣብያው ታስረው እንደሚገኙ ገልፆልናል፡፡

በተመሳሳይ መርካቶ የአዲስ አበባ ትልቁ የገበያ ማዕከል ውስጥ የቤት ቁሳቁሶች በአነስተኛ ሱቅ እየሸጠ የሚተዳደር አንድ የትግራይ ተወላጅ ወጣት እና በራይድ ታክሲ ሹፌርነት የሚተዳደር አንድ የትግራይ ተወላጅ ወጣት ከሳምንት በፊት ከአራዳ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው ተክለሀይማኖት አካባቢ ታፍሰው ሜክሲኮ አከባቢ ወደ ሚገኝ 5ኛ ፖሊስ ጣብያ ተወስደው እስከ አሁን በእስር እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለድርጅታችን የሰጡት መረጃ ያሳያል፡፡ ታሳሪዎቹ እስካሁን ለፍርድ ቤት አልቀረቡም፣ የተጠረጠሩበት ወንጀልም አይነገራቸውም በማለት ቤተሰቦቻቸው አሳውቀውናል፡፡

ድርጅታችን በተለይ ስማቸው እንዳይገለፅ የነገሩን የመምሪያ ፖሊሶች የጠየቀ ሲሆን የእስሩ ምክንያት ከላይ የመጣ እንደሆነ፣ እስሩ የሚፈፀመው ወቅታዊ ጉዳይ በሚል እንደሆነ፣ እነሱ ግን ምክንያቱን እንደማያውቁት ነግረውናል፡፡ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ በበተለይ ትግርኛ ተናጋሪ ወጣቶች ኤርትራውያንም ጨምሮ ትኩረት ያደረገ የዘፈቀደ እስር እየተፈፀመ እንደሆነ ተቋማችን አረጋግጧል፡፡ የኤርትራውያን እስር የቆየ ቢሆንም የትግራይ ተወላጆች ላይ ግን ከሰኔ ወር 2017 ዓ.ም መጀመሪያ ሳምንት አከባቢ ጀምሮ ተጠናክሮ የቀጠለ ነው፡፡

በዚም ምክንያት በርካታ የትግራይ ወጣቶች በትግራይ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የግጭት ስጋት ሸሽተው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም የዘፈቀደ እስር ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ብሔርን መሠረት ያደርገ የዘፈቀደ እስር ዜጎች በአገራቸው ተረጋግተው በእኩልነት እንዳይኖሩ የሚያደርግ ከመሆኑ በላይ የሚከተሉትን የአገሪቱ እና አገሪቱ የተቀበለቻቸው የአለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ ነው።

የተጣሱ የሕገ መንግስት ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች

1. በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 17 “ማንኛውም ሰው ነፃነቱን አያጣም፣ በሕግ ከተደነገገው ውጭ ሊያዝ፣ ሊታሰር አይገባም”።

2. በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 19(1)(3) የተያዙ ሰዎች የተያዙበት ምክንያት ወድያውኑ የማወቅ፣ በ48 ሰአታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው።

3. በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 25 ሁሉም ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በትውልድ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግበት እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፤

የሚሉ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ተጥሰዋል።

የተጣሱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች

1. ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት መግለጫ (UDHR) አንቀፅ 9 እና ዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት (ICCPR) አንቀፅ 6 ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን አያጣም፣ በሕግ ከተደነገገው ውጭ ሊያዝ፣ ሊታሰር አይገባም እንዲሁም አንቀፅ 26 ሁሉም ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በትውልድ፣ በማህበራዊ አመጣጥ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግበት ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው የሚሉ ድንጋጌዎች ተጥሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ስምምነት (ICCPR) መብቶች ፈራሚ ሀገር ስትሆን ስምምነቱ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 9(4) እና አንቀፅ 13(2) መሰረት የአገሪቱ የሕግ አካል ነው፡፡

በመንግስት ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ እርምጃዎች

1. የመንግስት አካላት በተለይም የአዲስ አበባ ፖሊስ በትግራይ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ተደጋጋሚ እስር እና እንግልት እንዲያቆም፣ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈታ፣ በወንጀል የሚያስጠረጥራቸው ጉዳይ ካለም በሕጉ መሠረት ለፍ/ቤት እንዲያቀርብ በአጠቃላይ ለሕገ መንግስቱ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ተገዢ እንዲሆን እንጠይቃለን፡፡

2. የዘፈቀደ እስር በትግራይ ተወላጆች ላይ እንዲከናወን የወሰኑ፣ ትዕዛዝ የሰጡ እና እየፈፀሙ የሚገኙ አካላት ውሳኔያቸውንና ተግባራቸውን በመመርመር በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

3. በርካታ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች በትግራይ ክልል ውስጥ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የግጭት ስጋት ሸሽተው አዲስ አበባ እየመጡ ሲሆን መንግስት ዜጎቼ ናቸው በማለት የኢኮኖሚና የማህበራዊ ድጋፍ በማድረግ እንዲያቋቁማቸው እና ለተለያዩ የሰው ንግድ ጨምሮ የወንጀል ተጋላጭነታቸው እንዲቀንስ ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ

Human Rights First – Ethiopia

Make Human Rights the Center of Decision!!

Scroll to Top