ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሰዎች መሰረታዊ መብትና ነፃነት እንዲከበር ቁርጠኛ አቋም ያለን ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኤርትራ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች እንዲሁም በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ እስርና ወከባ ሪፖርቶችን በተመለከተ በከፍተኛ ሁኔታ ያሳሰበን መሆኑን እንገልፃለን።
በኤርትራ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ላይ በስፋት እና በተደራጀ ሁኔታ በዘፈቀደ ለተራዘመ እስር እየተዳረጉ እንደሚገኙ ከተለያዩ አካላት ሪፖርት በዝርዝር ቀርቦልናል። እንደ ምንጮቻችን ከሆነ እስራቶቹ በዘፈቀደ የተፈፀሙ በመሆናቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊፈጠር ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል። ቅሬታ አቅራቢዎች ይህንን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልፀው ድርጅታችን እነዚህን ክስተቶች በማጣራት ተጨማሪ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄ አቅርቧል።
ድርጅታችን ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሪፖርቶች ያገኘ ሲሆን በቅድመ ምርመራው መሰረት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የኤርትራ ዜጎች ያለአግባብ በተለያዩ ፖሊስ ጣብያዎች ታስረው እንደሚገኙ አረጓግጧል። በተጨማሪም በቅርብ ጊዜያት የትግራይ ተወላጆች በተወሰኑ ቦታዎች በተመሳሳይ በዘፈቀደ እየታሰሩ መሆኑን ሪፖርቶች ደርሰውናል።
ስለሆነም ጉዳዪን መርምረን ሙሉ ሪፖርት እስክምናወጣ ድረስ ድርጅታችን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚከተለውን እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፦
1. ማንነትን መሰረት ያደረጉ እና የዘፈቀደ እስራት እንዳይፈጽም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ በተቋም ወይም በግለሰቦች ተፈፅመው ሲገኙም በአስቸኳይ እንዲያቆም ወይም እንዲያስቆም እና ታሳሪዎችን እንዲለቅ እንዲሁም የዘፈቀደ እስራቱን የፈፀሙ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲያደርግ፡፡
2. ቅድመ ሪፖርት መሰረት በማድረግ ኤርትራውያንና የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ ሁሉም ግለሰቦች በኢትዮጵያ ሕገ መንግስትና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች መሰረት ብቻ እንዲያስተናግድ፤ በተለይም ታሳሪ ግለሰቦች ክሳቸውን የማወቅ መብት፣ የመጎብኘት መብት፣ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት የመቅረብ መብት፣ በጠበቃ የመወከል መብት፣ እና ከህገ-ወጥ ወይም ከዘፈቀደ እስራት ጥበቃ እንዲሰጥ።
3. በሪፖርቱ የተደረገ ማንነት ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ እስራት ላይ ግልፅ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ እና ለተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ።
4. ስደተኞች፣ ፍልሰተኞችና ሌሎች ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት መብታቸውንና ክብራቸውን በኢፌዲሪ ህገ መንግስት፣ የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1110/2011 እና ኢትዮጰያ ያፀደቀችው የ1951 ዓለም ዓቀፍ የስደተኞች ስምምነትን መሰረት በማድረግ ለማስከበርና ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።
በመጨረሻም እየተደረገ ባለው የዘፈቀደ እስራት በከፍተኛ ሁኔታ እያሳሰበን የሚገኝ ጉዳይ መሆኑን በድጋሚ እየገለፅን መንግስት የሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር፣ ለማስጠበቅ እና ተጨማሪ ጥሰቶችን ለመከላከል አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ እየጠየቅን እነዚህ ቅድመ ሪፖርቶችን መሰረት በማድረግ ሙሉ ሪፖርት በማውጣት የዘፈቀደ እስራት ለመከላከልና መንግስት የእርምትና የተጠያቂነት እርምጃዎችን እንዲወስድ ክትትልና ውትወታ የምናደርግ መሆናችን እናረጋግጣለን።
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ
የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም
Human Rights First – Ethiopia
Make Human Rights the Center of Decision!!
