መግቢያ፡-
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ (Human Rights First Ethiopia) በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በቁጥር 4118 በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ደርጅት የተመዘገበና እውቅና ያገኘ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እየሠራ ይገኛል። አሁንም የኢምግሬሽን ዜግነት አገልግሎት የትግራይ ተወላጆች ፓስፖርት አሰጣጥ በተመለከተ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተገኘ መረጃ መሠረት መረጃውን በመመርመርና እንደሚከተለው አጭር ሪፖርት በማጠናቀር አቅርቧል።
በኢፌዲሪ ህገ መንግስት ዓንቀፅ 6 መሰረት ወላጆቹ/ወላጆቿ ወይም ከወላጆቹ/ወላጆቿ አንደኛቸው ኢትዮጵያዊ /ኢትዮጵያዊት የሆነ የኢትዮጵያ ዜጋ ነው/ ናት በሚል በህገ መንግስቱ በግልፅ የተመላከተ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በህገ መንግስቱ ዓንቀፅ 33 የዜግነት መብቶች ላይ ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ከፈቃዱ ውጭ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ሊገፈፍ እንዳማይችል የተገለፀ ሲሆን በተጨማሪም ደግሞ ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የኢትዮጵያ ዜግነት በህግ የሚያስገኘውን መብት፣ ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት አለው፡፡ በዝርዝር በወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች የሚያገኙት መብት ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት በዜግነቱ የሚገኙት ሁሉም መብቶች ማግኘት እንዳለበት የሚታወቅ ነው፡፡
በህገ መንግስቱ ዓንቀፅ 25 መሰረት ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ በመካከላቸውም ማነኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሄር፣ ብሄረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖሎቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት. በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡
የኢምግሬሽን ዜግነት አገልግሎት በፓስፖርት አሰጣጥ በተመለከተ የተሰራ የምርመራ ሪፖርት
የኢምግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ለዜጎቹ ዜግነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዋናነት ደግሞ ዜጎች ወደ ሚፈልጉት አገር እንዲጓዙ የግድ ፓስፖርት ስለሚያስፈልጋቸው በሃገሪቷ ህጎች መሰረት የመስጠት ግዴታ ያለበት ሲሆን መ/ቤቱ ይህንን ሲያደርግ ደግሞ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መሰረታዊ የዜጎች እኩልነት መብት በማድረግ እና በምንም መለክያ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ ማስተናገድ እንዳለበት የሚታወቅ ነው፡፡
ኢምግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ለኢትዮጵያ ዜጎች ፓስፖርት ለመስጠት ያስቀመጠው መስፈርት በጣም ግልፅና አጭር ሆነ በድህረ ገፁና በሌሎች የትስስር ገፆች ተገልፆ ይገኛል፡፡
መስፈርቶቹም ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያገለግሉ ሲሆን እነዚህም 1ኛ የተረጋገጠ የልደት ምስክር ወረቀት 2ኛ የታደሰ የቀበሌ መታወቂያ እና ሌሎች በኦንላይን መመዝገብና ከፍያ መፈፀም የሚሉ ናቸው፡፡
ከላይ የተገለፀው መሰረታዊ መርህ የኢምግሬሽን ዜግነት አገልግሎት ማክበር የሚጠበቅበት ቢሆንም ድርጅታችን ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች በተለያዩ ቀናት በመ/ቤቱ በመገኘት የፓስፖርት አሰጣጡ ምን ይመስላል በሚል ፓስፖርት ለመውሰድ ከትግራይ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በአካል በማነጋገር ከሌሎች ዜጎች በተለየ መልኩ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ የሆነ እንግልት፣ ወከባ እና ማስፈራራት እየደረሳቸው የሚገኝ ስለመሆኑ በምርመራ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
ድርጅታችን የምርመራ ሪፖርቱን ለመስራት ከመ/ቤቱ ሰራተኞች ጋር የፓስፖርት አስጣጡ በተመለከተ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተነገግረናል፣ በአካል በመ/ቤቱ በመገኘት አገልግሎቱን ተመልክተናል እንዲሁም ከ20 በላይ ተገልጋዮች አነጋግረናል ፡፡
ዝርዝር ግኝቶች
በመጀመሪያ የራሳቸው ፣ የአባታቸው ወይም የአያታቸው ስም የትግራይ ክልል ተወላጅ የሚመስል ያለባቸው የፓስፖርት አገልግሎት ጠያቂዎች በሙሉ 07 ቁጥር ወደ ሚባል ቢሮ እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ 07 ቁጥር ውስጥም ትግርኛ በሚናገሩ ሰራተኞች ምርመራ የሚደረግባቸው ሲሆን በየቀኑ ሰዎች በምልልስ እና እንግልት ብዛት እያለቀሱ ማየት የተለመደ ነው፡፡
ይህ የምርመራ ሪፖርት ስናዘጋጅ ወደ አስር የሚሆኑ ከትግራይ ክልል ፓስፖርት ለመውሰድ የመጡ እንዲሁም ደግሞ በአዲስ አበባ እና ሌሎች ክልሎች ተወልደው ያደጉ እና ለረዥም ዓመታት የኖሩ ግለሰቦች አነጋግሯል፡፡
ቃለ መጠየቅ የተደረገባቸው ግለሰቦች ደህንነት ሲባል የግለሰቦች ስም የተቀየሩ መሆኑ እንዲታወቅ እየገለፅን የተወሰኑት ታሪኮች ለማሳያነት ከታች አስቀምጠናል፡፡
አቶ ገብረክርስቶስ ( ስም የተቀየረ) በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ በፍትህ ሚኒስቴር በዓቃቤ ህግነት ተቀጥረው በመስራት ላይ የሚገኙ ሲሆን እንደ ማነኛው ኢትዮጵያዊ ፓስፖርት ለማውጣት በማሰብ ሁሉም ፓስፖርት ፈላጊ እንደሚያደርገው በኦንላይን ማመልከቻ በመሙላት ወራትን በመጠባበቅ ወረፋው ከደረሳቸው በኃላ ፓስፖርታቸው ለመውሰድ አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎች ግን ያልጠበቁት እና አብዛኛው የትግራይ ተወላጅ እየገጠመው ያለ ችግር እንደገጠማቸው ነግረውናል፡፡ በወቅቱ የተገለፀላቸው አንተ ኤርትራዊ ነህ ስለዚህ የኢትዮጵያ ፓስፖርት አይገባም የሚል በትልቁ የኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስቴር መ/ቤት ለሚሰራ ሰው እጅግ አስደንጋጭ እና የሚያበሳጭ እንደነበረ የደረሳቸው ወከባና እንግልት በመግለፅ ምስክርነታቸው ሰጥተውናል፡፡ በወቅቱ እሳቸው በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሰሩ ስለመሆናቸው በዝርዝር ለማስረዳት ጥረት ቢያደርጉም ኤርትራዊ ነህ ከሚል ምላሽ የተለየ መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
አቶ ገብረክርስቶስ ኤርትራ ሄደው የማያውቁ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት ኤርትራዊ ሊያስመስል የሚችል የትግርኛ ቅላፄ የላቸውም፡፡ በአገሪቱ ትልቁ መ/ቤት የሚሰራና እዛ እንደሚሰራ ማረጋገጫ ያለው ግለሰብ ኤርትራዊ ነህ በሚል ተልከሻ ምክንያት የዜግነት መብቱን የሚያጣ ከሆነ ሌላው ተራ የትግራይ ተወላጅ ምን ሊገጥመው እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በፍትህ ሚኒስቴር ዓቃቤ ህግ ሆኖ ለመቀጠር በዜግነት ኢትዮጵያዊ መሆን አንድ መስፈርት እንደሆነ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ መቋቋምያ አዋጅ 943/2008 ዓንቀፅ 11 (2) (መ) መሰረት በግልፅ የተመላከተ ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም አንድ በፍትህ ሚኒስቴር የሚሰራ ዓቃቤ ህግ ፓስፖርት መከልከል ማለት በትግራይ ተዋላጆች ላይ የሚደርሰው እንግልት ትልቅ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ተግባር ነው፡፡
አቶ ገብረክርስቶስ ከተደጋጋሚ ምልልስ በኃላ ይህ ሪፖርት ከመውጣቱ በፊት ፓስፖርቱን ስለማግኘታቸው ጠይቀናቸው ከብዙ ውጣ ውረድ በኃላ አሁን ፓስፖርታቸው ያገኙ ስለመሆናቸው ገልፀውልን ነገር ግን አሁኑም በትግራይ ተወላጆች እየደረሰ ያለው በህግ ያልተቀመጠ መስፈርት እንደሚያሳስባቸው በመግለፅ ጉዳዩ መፍትሄ የሚያስፈልገው ስለመሆኑ ገልፀውልናል፡፡
2ኛው ያነጋገርናቸው አቶ አፅበሃ ገብረ ( ስም የተቀየረ) የተባሉ በስልሳዎቹ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ አዲስ አበባ መኖር ከጀመሩ ከ 33 ዓመታት በላይ የሆናቸው ሲሆን ካናዳ የሚገኙትን ቤተሰቦቻቸው ለመጠየቅ ፓስፖርት በመፈለጋቸው በቀጠሮዋቸው መሰረት ወደ ኢምግሬሽን ቢሄዱም አብዛኛው የትግራይ ተወላጆች የሚገጥማቸው ችግር የገጠማቸው ሲሆን የአባታቻው እና እናታቸው መታወቅያ እንዲያመጡ የተጠየቁ ሲሆን ወላጆቻቸው በሂወት የሌሉ መሆናቸው ቢገልፁም መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ሌሎች በሂወት የሌሉትን የአጎቴ እንዲሁም የአክስቶቼ መታወቅያ እንዲያመጡ በመጠየቅ ለከፍተኛ የሆነ እንግልት ዳርጓቸዋል፡፡ በስተመጨረሻም እስከ ዳይሬክተር ድረስ አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሚ በማጣታቸው አገር አልባ እንደሆኑ እንደተሰማቸው በበስጭት ያጋጠማቸውን አጫውቶብናል፡፡ ይህ ታሪክ የሺዎች የትግራይ ተወላጆች በአሁኑ ሰዓት እያጋጠማቸው ያለ ህገ ወጥ ተግባር ሲሆን በህገ መንገስቱ ዓንቀፅ 25 የተቀመጠውን የዜጎች የእኩልነት መብት የሚጥስ ተግባር ነው፡፡
3ኛ አደይ ለተብርሃን በአዲስ አበባ ከ 40 ዓመት በላይ የኖሩ የ70 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ ኢንግሊዝ አገር ለንደን የምትገኘው ልጃቸውና የልጅ ልጆቸው ለመጠየቅ ፓስፖርት የግድ ስላስፈለጋቸው ፓስፖርት እንዲሰጣቸው ለኢምግሬሽናና ዜግነት አገልግሎት ቢያመለክቱም ከአስርት ዓመታት በፊት የሞቱትን ወላጆቻቸው የቀበሌ መታወቂያ እንዲያመጡ የተገደዱበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ከሆኑ በብዛት ከሚፈፃሙ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡ እሳቸውም ወላጆቻቸው በህይወት እንደማይገኙ ገልፀው የተወለዱበት እና ያደጉበት ወረዳ፣ ቀበሌና ጎጥ በመግለፅ ፓሰፖርት እንዲሰጣቸው በተደጋገሚ ቢያመለክቱም የሚሰማቸው አጥተው ፓስፖርት ባለመውሰዳቸው ልጃቸውና የልጅ ልጆቻቸው መጎብኘት ሳይችሉ ቀርቷል፡፡ የዜግነትና ኢሚግሬሽን አግልግሎት ወላጆቼ በህይወት የሉም በማለታቸው የአጎቶቻቸው መታወቂያ እንዲያመጡ የተገለፀላቸው ሲሆን ወደ ትግራይ ከሄዱ ረዥም ግዜ እንደሆናቸው በህይወት የቀረ አጎት እንደሌላቸው ቢገልፁም በትግራይ ስለተወለዱ እና ስማቸው የትግርኛ ስለሚመስል ብቻ ፓስፖርት የማግኘት መብታቸው ከተነፈጉት በሺዎች ከሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች አንዷ ሆነው ይገኛሉ፡፡
ከትግራይ ውቅሮ ከተማ የመጣ የ19 ወጣት ብርሃን ( ስም የተቀየረ) በግቢው ውስጥ እያለቀሰች ነው ያገኘናት፡፡ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ባወጣው መስፈርት መሰረት የልደት ምስክር ወረቀት፣ የቀበሌ መታወቅያ ይዛ የመጣች ቢሆንም የ8ኛ ክፍል የትምህርት ማስረጃ እና የወላጆቿ መታወቅያ እንድታመጣ ስለተነገራት ተመልሳ ይዛ መጥታለች፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ሁሉ ማስረጃ ከቀረቡ በኃላም አገልግሎት ሊሰጣት አልቻለም፡፡ የ3ኛ እና የ4ኛ ክፍል የትምህርት ማስረጃ አምጪ የሚል ሌላ አዲስ መስፈርት በመጠየቅ ሊሰጧት አልቻሉም፡፡ ትምህርት ቤቱ የተቃጠለና የተዘረፈ በመሆኑ አሁን ማስረጃው አይገኝም ብሎ ለማስረዳት ብትሞክርም ሰሚ የለም፡፡
ሌሎች በኦሮሚያ ክልል፣ አማራ ክልል ጎንደር ተወልደው ያደጉ እና የአያታቸው ስም የትግራይ ስለሚመስል ብቻ ተመሳሳይ የሆነ እንግልት ሲደርስባቸው ተመልክተናል፡፡
የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽን አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚገኙ ሌሎች ፓስፖርት ፈላጊዎች እና የትግራይ ተወላጆች ላይ ፓስፖርት ለማግኘት እጅግ የተለያዩ እና የተራራቁ አሰራሮች እየተከተሉ ይገኛሉ፡፡ የትግራይ ተወላጆች ፓስፖርት ለማግኘት ያለው ውጣ ውረድ እጅግ በጣም ከባድ መሆኑን በአካል በማየት እና ምስክሮች በማነጋገር ተገንዝበናል፡፡ አንዳንድ የመ/ቤቱ ሰራተኞች ለሰው ልጅ ምንም ዓይነት ክብር የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ ተገልጋዮችን በማስፈራራት የሚሳደቡ ጭምር ያሉበት መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ማጉላላት መፍጠር የሚያስቀድሙ መሆኑን ተገንዝበናል፡፡
መጠኑ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከፍ ያለ ቢሆንም ይሄ ችግር ከትግራይ ተወላጆች በተጨማሪ በሶማሊ ክልል ተወላጆችም ጭምር እንዳለ ከሶማሊ ተወላጅ ተገልጋዮች መረዳት ችለናል፡፡ ዝርዝር ምርመራ ካደረግን በኃላ ግልፅ የምናደርገው ይሆናል፡፡
የተፈፀሙ የሕግ እና የመብት ጥሰቶች እና ተያያዥ ግዴታዎች
1ኛ የህገ መንግስቱ ዓንቀፅ 33 የዜግነት መብቶች
በህገ መንግስቱ ዓንቀፅ 33 የተመለከተው የዜግነት መብቶች ላይ ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ከፈቃዱ ውጭ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ሊገፈፍ እንዳማይችል የተገለፀ ሲሆን በተጨማሪም ደግሞ ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የኢትዮጵያ ዜጋ የኢትዮጵያ ዜግነት በህግ የሚያስገኘውን መብት፣ ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት አለው፡፡
በዚህ ረገድ የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ የኢትዮጵያ ዜግነት በህግ የሚያስገኘው መብት፣ ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት በእኩልነት ማግኘት አልተቻለም፡፡
2ኛ የህገ መንግስቱ ዓንቀፅ 25 የእኩልነት መብት
በህገ መንግስቱ ዓንቀፅ 25 መሰረት ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ በመካከላቸውም ማነኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሄር፣ ብሄረሰብ፣ በቀለም፣ በፆታ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖሎቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት. በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው፡፡
ከላይ የተገለፀው በዜጎች መካከል ምንም ዓይነት ክልከላ እንዳይኖር የሚከለክለውን የህገ መንግስቱ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት መርህን የጣሰ ነው፡፡
3ኛ የሕገ መንግስቱ ዓንቀፅ 32 የመዘዋወር መብት
አንድ ሰው በዜግነቱ ፓስፖርት የማግኘት መብት አለው፡፡ በዋናነት ፓስፖርት የሚያስፈልገው በውጭ ሃገር ለትምህርት፣ ለህክምና፣ ለጉብኝት፣ ለስራ እና ለሌሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች ለመጓዝ ሲሆን በተዘዋዋሪ ፓስፖርት እንዳይሰጥ በመከልከል የመዘዋወር ነፃነት መገደብ ነው፡፡
በአጠቃላይ የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች ዜጎች ተለይተው በማንነታቸውና ፓስፖርት እንዳያገኙና በሃገራቸው እንደ 3ኛ ዜጋ የመታየት ጉዳይ መቆም ያለበት እና በህገ መንግስቱ የተረጋገጠላቸውን የዜግነት መብታቸው በእኩል ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዲከበር ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩና መፍትሄ እንዲያመጡ፡፡
የኢምግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት እና የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል ተቋማት ሊወሰዱ የሚገባቸው መፍትሔዎች
- በህገ መንግስቱ ዓንቀፅ 6፣25፣ 32 እና 33 የተገለፁት መሰረታዊ የሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች እንዲከበር እንዲሰራ
- የትግራይ ተወላጅ ፓስፖርት ፈላጊዎች ለሁሉም ዜጎች በወጣው መስፈርት ብቻ በእኩልነት አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲደረግ እና ልዩነቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንዲያደረግ
- ችግሮች የሚቀርፉና ተገቢ ማጣራት ለማድረግ የሚያግዙ አሰራሮች በመዘርጋት ከሌሎች ዜጎች እኩል የሆነ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ፡፡ በቅርበት ለማጣራት እና አገልግሎት ለመስጠት ይችል ዘንድ በትግራይ ክልል መቐለ ቅርንጫፍ አዲስ የፓስፖርት መስጠት አገልግሎት እንዲጀምር እንዲደረግ
- የመ/ቤቱ ሰራተኞች በዘፈቀደ የሚጠዩቁት ቀድመ ኩነት ለማስቀረት ግልፅ እና አንድ ወጥ የሆኑ አሰራሮች የሚፈጥር መመሪያ ወይም ህግ እንዲዘረጋ እንማፀናለን፡፡
ከላይ የተገለፁት ማሻሻያዎችና የመፍትሄ እርምጃዎች የኢምግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት በተቻለ ፍጥነት እንዲወስድ እየጠየቅን ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ይህ የእኩልነት መርህ የሚጥስ፣ የዜግነት መብት የሚገፍፍ አሰራር እንዲታረም ጉዳዩ መሰረታዊ የዜጎች መብት ጥሰት በመሆኑ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 መሰረት ወደ ፍ/ቤት እንደምንሰደው ለመግለፅ እንፈልጋለን፡፡
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ
Human Rights First Ethiopia
ሐምሌ 2016 ዓ/ም
