ታሕሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም
መግብያ
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች ኢትዮጵያ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሠረት በኢፌዴሪ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በቁጥር 4118 በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ደርጅት የተመዘገበና እውቅና ያገኘ ሲሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ እየሠራ ይገኛል። የዚህ አካል የሆነው በአክሱም ከተማ በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ የተፈፀመ የመብት ጥሰት ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተገኘ መረጃ መሠረት እንደሚከተለው አጭር ሪፖርት በማጠናቀር አቅርቧል።
የአክሱም ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ተቃውሞ መነሻና የመብት ጥያቄ
በአክሱም ከተማ የተለያዩ የመንግስትና የግል የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ይህ ሪፖርት የሚያተኩረው በዋናነት በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ነው፡፡ ይህ ሪፖርት ለማጠናከር ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ፣ አስተማሪዎች እንዲሁም የተማሪ ወላጆች በመጠየቅ ጉዳዩን በማጣራትና በመመርመር ሪፖርቱ ተዘጋጅቷል፡፡ ሒጃብ ለመከልከል የሚያስችል መነሻ ሕግ ወይም ደንብ ካለ እና ሌሎች መረጃዎች ለማጣራት የአክሱም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርእሰ መምህር ለመጠየቅ ጥረት ያደረግን ሲሆን ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው አስተያታቸው ማካተት አልተቻለም፡፡ በአክሱም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ( አሁን ሁለት ት/ቤት ሁኗል)፣ በወርዒ 2ኛ ደረጃ ት/ቤትና ሙሱሊም ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸው ለሶስት ሳምንት ገደማ አቋርጠው የሚገኙ ስለመሆናቸው ባደረግነው ማጣራት ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
ቅድመ ጦርነት የነበረው የአክሱም 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተማሪዎች የአለባበስ ስርዓት
በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶችና 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከጦርነቱ በፊት (ከጥቅምት 2013 ዓ/ም በፊት) የነበረው የአለባበስ ህግና ስርዓት ማነኛውም ተማሪ ከትምህርት ቤት ዩኒፈርም ውጭ ምንም ዓይነት ሻርፕ፣ ሂጃብ እና የመሳሰሉት አልባሳት ለብሶ ወደ ትምህርት ቤቶች መግባት የማይፈቀዱ የነበሩ ስለመሆናቸው ተማሪዎች፣ ሙስሊም ሴት ተማሪዎችና አስተማሪዎች ገልፀውልናል፡፡ ስለሆነም ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ አድርገው መማር ይከለከሉ የነበሩ መሆኑን እና የማይፈቀድ የነበረ ስለመሆኑ ነግረውናል፡፡
ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ማግስት የመብት ጥያቄ እሰከተነሳበት ግዜ የነበረው የአለባበስ ስርዓት
ከላይ እንደተገለፀው ቀደም ብሎ ማለትም በትግራይ ክልል ከነበረው ጦርነት በፊት ሂጃብ ለብሶ መማር የማይፈቀድ የአለባበስ ስርዓት የነበረ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ነግረውናል፡፡ ከጦርነቱ በኃላ ለሶስት ዓመታት ገደማ በክልሉ በነበረው ጦርነት ትምህርት ተቋርጦ ዳግም ሲጀመር ተማሪዎች ቀስ በቀስ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሰ ጀምረዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች የአለባበስ ስርዓት የኒፎርም ጨምሮ ከጦርነቱ በፊት የነበረው ችላ ስለተባለ ተማሪዎች ያለ ዩኒፎርም የመማር ማስተማር ስራው መቀጠሉ እንዲሁም ሴት ሙስሊም ተማሪዎችም ሂጃብ በማድረግ ትምህርታቸው መቀጠላቸውንና በአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ሲተገብሩት የነበረው የአለባበስ ስርዓት ተቋርጦ የቆየ ስለመሆኑ ነግረውናል፡፡
ነባሩ የአለባበስ ስርዓት መተግበር መጀመርና የመብት ጥያቄ መነሳት በተመለከተ
የዘንድሮ 2017 ዓ/ም የትምህርት ዘመን መጀመር ጋር ተያይዞ በተለይም በአክሱም 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከጥቅምት 05/ 2017 ዓ/ም ጀምሮ ሂጃብ አድርጋችሁ መምጣትና መማር አትችሉም የሚል መልእክት ሲተላለፍ የነበረ ስለመሆኑ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች እና አስተማሪዎች ነግረውናል፡፡ ነገር ግን በት/ቤቱ የወረደ መመሪያ ሳይተገበር ከቆየ በኃላ ታህሳስ 06/2017 ዓ/ም የሁሉም ተማሪ ወላጆች ጥሪ ተደርጎ ስለነበር ከዛሬ በኃላ ሒጃብ ለብሶ መግባት ይከለከላል የሚል መመሪያ ለወላጆች ተነግሯል፡፡ የሙስሊም ሴት ተማሪዎችና ወላጆች ይህ ህግ ተገቢ አለመሆኑንና ሃይማኖታዊ ግዴታችን የሚጥስና መብታችን የሚጋፋ ስለሆነ በቂ ምላሽ ሊሰጠን ይገባል የሚል ጥያቄ ቢጠዩቅም ጥያቄው በስብሰባው መጨረሻ የተነሳ በመሆኑ ተገቢ ትኩረትና ምላሽ በትምህርት ቤቱ አመራር ሳይሰጥበት ስበሰባው ተጠናቋል፡፡ ከታህሳስ 08/ 2017 ዓ/ም ጀምሮ ተማሪዎች ሂጃብ አድርገው መግባት በአንዳንድ ክፍሎች እንደተከለከለ፣ በአንዳንድ ክፍሎች ደግሞ በተወሰኑ መምህራን መልካም ፈቃድ ሒጃብ ለብሰው ትምህርታቸው መቀጠላቸው ከተማሪዎች እና አስተማሪዎች ቃል ተረድተናል፡፡ በሚቀጥለው ቀን ማለትም እሮብ ታህሳስ 09/ 2017 ዓ/ም ግን ሂጃብ የለበሱ ሴት ሙስሉም ተማሪዎች ከሰልፍ እንዲወጡ መደረጋቸውን በሚቀጥለው ቀን ማለትም ታህሳስ 10/2017 ዓ/ም ግን ሂጃብ ያደረጉ ተማሪዎች ከበር እንዲመለሱ የተደረጉ ሲሆን ከዛን ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለጉዳዩ መፍትሄ ባለመሰጠቱ ትምህርታቸው አቋርጠው የሚገኙ ስለመሆናቸው ለተቋማችን ምስክርነታቸው የሰጡ ሴት ሙስሊም ተማሪዎችና ገልፀውልናል፡፡ ይህንንም ከአስተማሪዎች ጭምር አረጋግጠናል፡፡
የተማሪዎች የመብት ጥያቄ ለሚመለከተው የከተማው የአስተዳደር አካላት ማቅረብ
በአክሱም 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ከበር እንዲመለሱ ከተደረጉ በኃላ መብታቸው እንዲከበር ለሚመለከታቸው የአክሱም ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት የሃይማኖት ጉዳይ የሚመለከታቸው ኦፊሰር መ/ር ሙሉ የተባሉ ሰራተኛ ማናገራቸውና ህጉ በወመህ (ወላጅ መምህራን ህብረት) የፀደቀ ህግ ነው ነባር ህግ ነው የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልፀውልናል፡፡ በመቀጠል ጥያቄዎቻችን በመያዝ ለአክሱም ከተማ ት/ቤት ፅ/ቤት እንዲሁም ለማእከላዊ ዞን አስተዳደር አመልክተው በቂ ምለሽ ያላገኙ ስለመሆናቸው ነግረውናል፡፡
የተማሪዎች እስርና ወከባ
የመብት ጥያቄ ያነሱ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች ከአክሱም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 20 ተማሪዎች ወደ ፖሊስ ጣብያ ተወስደው የነበረ ሲሆን አብዛኞቹ ወዲያውኑ የተለቀቁ ሲሆን 3 ተማሪዎች ግን ለሶስት ሰዓታት ታስረው የተለቀቁ ስለመሆናቸው ታስረው ከነበሩ ሴት ተማሪዎች በማነጋገር ተረድተናል፡፡ ፖሊሶች ሶሰትና ከዛ በላይ ሆነን ስንሄድ ያስፈራሩናል በማለትም ጨምረው ገልፀውልናል፡፡
ከወላጆች ፍላጎት ውጭ በቀጠና አመራሮች ስብሰባ መጥራትና ማዋከብ
የመብት ጥያቄ ከተነሳበት ግዜ ጀምሮ በየቀጠናው የሚገኙ የቀጠና አስተዳደር አካላት ( በተለምዶ የልምዓት ጉጅለ በመባል የሚታወቁት) በየቀጠናው እየዞሩ የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር ሴት ሙሱሊም ተማሪዎች ያላቸው ወላጆች ቤት ለቤት በመዞር ስበስባ አለ፣ እርዳታ አለ እና ሌሎች ሰበቦች በመፍጠር ልጆቻቸው እነዲመክሩ በነባሩ ህጉ ነው መማር ያለባቸው በማለት ወላጆች በመሰብሰብ ለማሳመን እና የማስፈራራት ሁኔታዎች መኖራቸው ከተሰበሰቡ የተማሪ ወላጆች ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በተመለከተ
የሁሉም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መስተጓጎል እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች የፈተና ፎርም የሚሞላበት ወቅት በመሆኑና ፎርሙ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2017 ዓ/ም መሆኑ የገለፁልን ሲሆን የቀሩት ቀናት በጣት የሚቆጠሩ ስለሆኑ ተማሪዎች ለዓመታት የለፉበት ትምህርት እንዳይስተጓጎል ተገቢ ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በተለይም በአክሱም 2ኛ ደረጃ (በአንድ ግቢ የሚገኙ ሁለት ት/ቤቶች) እና ወርዒ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የሚገኙ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች መብታቸው ለማስከበር ጥያቄ በመጠየቃቸው ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው የሚገኙ ስለመሆናቸው ተማሪዎችና መምህራን አረጋግጠውልናል፡፡ ተማሪዎቹ ከቀን 08/04/2017 ዓ/ም ጀምሮ ሪፖርቱ እስከ ተጠናቀረበት ግዜ ጀምሮ ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው ይገኛሉ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምላሽ
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአክሱም ከተማ ትምህርት ቢሮ በቀን 22/04/2017 ዓ/ም የአለባበስ ስርዓት በተመለከተ የፃፈው ደብዳቤ ተመልክተናል፡፡ ከክልሉ እስልምና ጉዳዮች አቤቱታ የቀረበለት መሆኑን በመግለፅ ለአክሱም ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ በዚህ ጉዳይ ላይ አዲስ መመርያ ስላልወጣ አዲስ ክልከላ ይሁን አዲስ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፣ ስለዚህ በነበረው መቀጠል አለበት የሚል አሻሚ የሆነ ደብዳቤ እንደፃፈ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አክሱም 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት ተማሪዎች ሒጃብ አድርገው ለመማር የማይፈቀድላቸው የነበረ ሲሆን ከጦርነቱ በኃላ ትምህርት ሲጀመር ግን ተማሪዎቹ ሒጃብ እየለበሱ ነበር፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት የነበረ ሲባል ቅድመ ጦርነት የነበረ ነው ወይስ ከሰላም ስምምነት የነበረ ? የሚል አሻሚ ያደርጓል፡፡ ስለ ሒጃብ አለባበስ የሚመለከት የሕግ መሰረት ጠቅሶ በግልፅ ያስቀመጠው አቅጣጫ የለም፡፡
በአጠቃላይ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለአክሱም ከተማ የፃፈው ደብዳቤ ለችግሩ ግልፅ መፍትሄ የሚሰጥ ባለመሆኑ ችግሩ እስከአሁን እንዲቀጥል አስተዋፀኦ አድርጓል፡፡
የተፈፀሙ የሕግ እና መብቶች ጥሰቶች
1. በሃይማኖት ምክንያት የመማር መብት አድልዎ በመፈፀሙ ምክንያት በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 25 የተደነገገውን የእኩልነት መብት ተጥሷል
2. በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 27 የተደነገገውን የሃይማኖት የእምነትና የአመለካከት ነፃነት መብት ተጥሷል፡፡
3. የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው “ በትምህርት ተቋማት የአምልኮ ስርአት የሚመለከት መመሪያ ” እንደሚከተለው ይላል
“ የእስልምና እምነት ተከታይ ሴት ተማሪዎች ከዩኒፎርም ጋር የሚመሳሰል ሒጃብ ማድረግ ይችላሉ፣ ከሒጃብ በቀር ሙሉ ጥቁር ልብስ ሙሉ በሙሉ ፊትን ጨምሮ የመሸፍን ወይም “ኒቃብ” በትምህርት ተቋማት መልበስ አይፈቀድም ”
በዚህ መመሪያ መሰረት ከዩኒፈርም ጋር የሚመሳሰል ሒጃብ መልበስ የተፈቀደ መብት እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ስለዚህ በተለይ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከሕገ መንግስቱ በተጨማሪ የሚኒስቴሩ መመሪያ በመጣስ የፈፀሙት የመብት ጥሰት ነው፡፡
4. በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 17 (2) ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርዓት ውጭ ሊያዝ ወይም ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም በሚል የተገለፀው መሰረታዊ ሕገ መንግስታዊ ጥበቃዎች ተጥሰዋል፡፡
በክልሉ መንግስት ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ እርምጃዎች
1. የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ይህንን መሰረታዊ በሕገ መንግስት፣ አዋጅና መመሪያዎች የተደነገጉ መብቶች በመጣስ ትምህርት እንዲቋረጥ ባደረጉ አካላት ፣ ትእዛዝ የሰጡ እና ወደ ግቢው እንዳይገቡ የከለከሉ አካላት አጣርቶ አስተዳደራዊ እርምት እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡
2. የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ እና ፖሊስ ኮሚሽን ይህንን ጥሰት የፈፀሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ ምርመራ እንዲጀምር እንጠይቃለን
3. የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ይህንን መሰረታዊ የሴት ሙሱሊም ተማሪዎች መብት እንዲከበር ጉዳዩን በህግና ስርዓት ብቻ እንዲመራ እንዲሁም ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው በአፋጣኝ እንዲመለሱ በማድረግ በተለይም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፎርም የሚሞላበት ግዜ ስለሆነ በፍጥነት ፎርም እንዲሞሉ ተደርጎ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፡፡
4. የተማሪዎቹ ጥያቄ በአገር አቀፍና ክልሉ ባለው ህግ መሰረት ብቻ ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት በሕገ ደንቡ መሰረት ተማሪዎች ትምህርታቸው እንዲቀጥሉ በማድረግ መብታቸው እንዲከበር እንጠይቃለን፡፡
ቅድሚያ ለሰብአዊ መብቶች
Human Rights First





See insights and ads
All reactions:
